የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት አገልግሎት

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋነኛ ተልዕኮ ለከተማዋ ነዋሪዎች ንጹህ፣ አስተማማኝ እና ጥራቱን የጠበቀ የመጠጥ ውኃ በፍትሃዊነት ማቅረብ ነው። ድርጅታችን የከተማዋን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ታሳቢ በማድረግ፣ የውኃ አቅርቦቱን ለማሳደግ በከፍተኛ ትጋት እየሰራ ይገኛል።

 

1. የምንሰጣቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች

  • የአዲስ መስመር ዝርጋታ፦ አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ድርጅቶች እና የመንግስት ተቋማት የውኃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፈጣን የመስመር ዝርጋታ አገልግሎት እንሰጣለን።

  • የውኃ ቆጣሪ ተከላና ጥገና፦ ደረጃቸውን የጠበቁ የውኃ ቆጣሪዎችን መግጠም፣ ብልሽት ሲያጋጥም መጠገንና ዕድሜያቸውን የጨረሱትን መተካት።

  • የቴክኒክና ጥገና አገልግሎት፦ በዋና መስመሮችም ሆነ በቤት ውስጥ መስመሮች ላይ የሚከሰቱ የውኃ መፍሰስ (Leakage) እና የቧንቧ ስብራት ችግሮችን በሰልጠናቸው ባለሙያዎቻችን በፍጥነት መጠገን።

2. የውኃ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር

የማህበረሰባችን ጤና ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። በመሆኑም፦

  • ከምንጮችና ከጥልቅ ጉድጓዶች የሚቀዳው ውኃ ለተጠቃሚዎች ከመሰራጨቱ በፊት በዘመናዊ ላቦራቶሪ ጥብቅ የጥራት ምርመራ ይደረግለታል።

  • ውኃው ከጀርምና ከተለያዩ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን የጸዳ እንዲሆን የማከም (Chlorination) ስራ በየቀኑ ይከናወናል።

3. አቅርቦቱን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ የዝግጅት ስራዎች

ድርጅቱ አሁን ካለው አቅርቦት ባለፈ፣ የወደፊት የከተማዋን የውኃ ጥም ለመቆርጥ የሚከተሉትን መጠነ-ሰፊ ዝግጅቶች እያደረገ ይገኛል፦

  • አዳዲስ የውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮ፦ የውኃ ምርትን ለማሳደግ ተጨማሪ ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶችን ለመቆፈር ጥናቶች ተጠናቅቀው ወደ ተግባር እየተገባ ይገኛል።

  • የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች፦ ውኃ ባልደረሰባቸው አዳዲስ የከተማዋ ሰፈሮች የውኃ መስመሮችን ለመዘርጋትና ግዙፍ የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች (Reservoirs) ለመገንባት ዝግጅታችንን አጠናቀናል።

  • የቴክኖሎጂ ማዘመን፦ የውኃ ብክነትን ለመቀነስና አሰራራችንን ለማዘመን ዲጂታል የውኃ ቆጣሪዎችንና የዘመናዊ ቢሊንግ (Billing) ስርዓትን ለመተግበር በዝግጅት ላይ እንገኛለን።

4. የውኃ አገልግሎት ለማግኘት የሚረዱ መመሪያዎች

  • አዲስ የውኃ መስመር ለማስገባት የሚፈልጉ ደንበኞች የይዞታ ማረጋገጫ እና የመታወቂያ ኮፒ በመያዝ በድርጅታችን በአካል በመቅረብ ማመልከት ይችላሉ።

  • ማንኛውም የውኃ መቆራረጥ ወይም የቧንቧ ስብራት ሲያጋጥም በቅርብ ርቀት ለሚገኙ የዲስትሪክት ጽህፈት ቤቶቻችን ወይም በስልክ መስመሮቻችን በመደወል እንዲጠቁሙ እናሳስባለን።

“ንጹህ ውኃ ለሁሉም፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለጤናማ ማህበረሰብ!”

Scroll to Top